የ “የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው ”  እሣቤ እና የህፃናት ጉዳይ

ከ አንድ፡ ወዳጄ ጋር ተቀምጠን ፡ ሻይ እየጠጣን ሳለ ፡ ያው ፡ እናቶች ፡ ስንገናኝ  የወሬው ፡ ርዕስ ሁሉ ዞሮ ዞሮ ወደ ልጆቻችን ዙሪያ እንደመሆኑ ፡ ልጆቻችንን በጥናት ፡ ማገዝ ላይ ስናወራ ፡ የምትጠቀምበትን ዘዴ ፡ እያስረዳችኝ በዚህ ተረት ፡ ደገፈችው ።  ያው ፤ ታውቂ የለ ያገራችንን “የትም ፍጪው ፡ ዱቄቱን አምጪዉ?” “ስለዚህ ፡ ያው ውጤት ተኮር  መሆን ግድ ይላል” ፡ አለችኝ ። ይህን አባባል ፡ እንደ ተረት ፡ የማውቀው ቢሆንም ፡ ከነበርንበት ፡ ሁኔታ ፡ ከልጆች አጠናን ጋር ፡ ተያይዞ ፡መጠቀሱ ፡ እንደው እንዲሁ ፡ ሰምቼ  ፡ የማላውቀውን ያህል ፡ እጅግ ነካኝ ። ስለዚህ ፡ ይህን ፡ አባባል ፡ ምን ያህል ፡ በህፃናት ፡ ላይ ፡ ተፅዕኖ ፡ እንደምናሣድርበት ፡ በጥቂቱ ፡ ልል ፡ ወደድኩ። ከ 0-6 ባለው ፡ የ እድሜ  ክልል ላይ ፡ በመወሠን ፡ ከሞንቴሶሪ አስተምህሮ ጋር አነፃፅረን ፡ እስቲ ፡ በጥቂቱ ፡ እንቃኘዉ።

የትም ፍጪው ፡ ዱቄቱን አምጪው ፡ የሚለው ብሂል እርግጥ ፡ ነው የውጤትን ፡ አስፈላጊነት ፡ ያስተጋባል ። በአንዱ ፡ በኩል ፡ ምንም ዓይነት ዋጋ ፡ ይከፈል ፡ ግን ፡ ውጤት ይምጣ ፡ ነው ። በሌላ  ፡ በኩል ፡ ደግሞ ፡ የሚከፈለው ዋጋ ፡ ምንም ፡ ቢሆን (አካሄዱ መልካምም / ክፉም ) ዉጤቱን ማክበር ነው ፡ ይመስላል ። የት ፣  እንዴት ፣ ለምን ( መጠየቅ ) አያስፈልገንም ፡ ዉጤትን :ግብ: አርገን ፡ ወጥረን ፡ እንስራ ፤ ግን ይህ : አባባል ፡ በራሱ ፡ ግጭት የለውም ? እንዴ ከልብ ካሰብነው እኮ አለመፈጨት  ፣ መሸርከት ፣ በጣም መላም ፡ ሁሉም እኮ የመፍጨት ሙከራ ፡ ውጤት ሊሆኑ ፡ ይችላሉ ። ዉጤቱ 1 እና 1 ብቻ ፡ ነው ፡ ማለት ግን እነዚህ ፡ ሌሎች ፡ ውጤቶች ፡ እንዴት ፡ እንደመጡ ተረድተን ፡ ወደ ሌላኛዉ የ ዉጤት አይነት የምንሸጋገርበትን ፡ መፍትሄ እያበጀን ፡ ካልሄድን ፡ ከተግባር ፡ ተምረን ፡ የተለየ ፡ ውጤት ፡ ለማምጣት ፡ ያዳግተናል ወይም ውጤቱን ለመቀየር ምን ስልት ልጠቀም የሚለውን ምርጫ ድፍን ያደርግብናል። ለምሣሌ ፦ ይህን አባባል በህፃናት ዓለም ብናየው ፡ አንድ ፡ ከ ፫-፮ ዕድሜ ላለ ህፃን ፡ በዱቄት ልንመስለው ፡ የምንችለውን ነገር እናንሣ ፤ ፊደላትን መፃፍን = ዱቄታችን ነው እንበልና ፊደላትን ፡ አዙሮ ፡ መፃፍ ፡ ማንጋደድ ተመሳሳይ ዝርያዎችን ማቀላቀል ፡ በጣም ፡ የሚታይ ፡ ክስተት ነው ።

 ይህ ፡ ነገር ፡ በብዙ ወላጆች ዘንድ ፡ ” ፃፍ/ፊ ብዬሀለው/ሻለው! ፃፍ/ፊ! እያልን እጃቸውን በመያዝ ፣ በነጠብጣብ ፡ የተፃፉ ፡ ፊደላትን፡ እንዲያደምቁ ፡ በመግፋት ፣ ስንቴ ፡ አሣየሁህ እያልን ፡በማስደጋገም ፡ አልፎ ተርፎ ቁጣ ፣ ጩኸት ወይም ቅጣት በብዛት ፡ የምንጠቀምበት ፡ ዘዴ ፡ ነው ። በተጨማሪ ታድያ ፡ እኛም ፡ የልጆቹ  ፡ “እክል” የሚፈታው በግዜ ነው ፡ ሲያድግ ፡ ያስተካክላል / ታስተካክላለች በማለት  ትንሽ ታግለን እንተወዋለን። ከጊዜ ፡ ብዛት ፡ ዱቄቱ ፡ ይመጣል ፡ ማለት አይደል ? በተለይ ፡በብዛት ፡ የተመለከትኩት ፡ የህፃናትን ፡ እጅ ላይ ፡ እጅን ጭኖ አብሮ ፡ መፃፍ ስንለቃቸው ፡ ያንን ፡ እንዲደግሙ መጠበቅ የተለመደ ፡ ክስተት ነው ። እንዴትም ፡ ይፈጭ ፡ ዱቄቱ ይምጣ ። እንዴትም እናሣየው ፡ ህፃኑ ፡ ይፃፍ ።በቁጣም በዱላም በመተውም።

 ታድያ ፡ ሞንቴሶሪ ይህን ፡ የፅሁፍ ፡ ጣጣ የሚፈታበት ፡ እጅግ ፡ መልካም አካሄድ ፡ ቀይሳ ፡ እንዴት እንፍጭ የሚለውን አሣይታናለች ።

 ፅሁፍ : ከንባብ : ይልቅ : ከአንድ : ግለሠብ : የግል ሀሣብ የሚመነጭ : ድርጊት ነው ። ለምሣሌ ፦ አንድ ፅሁፍን እያገለበጥን : ካልሆነ በስተቀር ራሣችን ስንፅፍ : መጀመርያ : እናስበዋለን ያሠብነውን : በወረቀት እናሠፍረዋለን ። የምናስበው : በቋንቋ ነው : ያ : ቋንቋ ድምፀቶች አሉት። የድምፀቶቹ ስብስብ : ቃላትን ፣ የቃላቱ ስብስብ : ዓረፍተ : ነገርን የዓረፍተ ነገሩ ጥርቅም : አንጓን : እያለ : ከፊደል : ጀምሮ ፣ እስከ : ድርሰት / ግጥም : ይዘልቃል ። የፅሁፍ : መነሻ (cell) ፊደል ቢሆንም : ፊደል : ደግሞ : የድምፅ : መገለጫ ነው ። አንድ ድምፅ : በ symbol ( ቅርፅ ) ሲቀመጥ ፊደል : እንለዋለን ።

 እየተማርን ያለነው  በ ቋንቋችን ከሆነ አብዛኞቹን ድምፆች እናውቃቸዋለን ። ምክንያቱም   እናወራበታለን ወይም በዙሪያችን ሲነገር  እንሠማለን።  ስለዚህ ይህ በቤት የጀመረ የቐንቐ ሀብት በትምህርት ቤት ደግሞ ይበልጥ ይታገዛል። አንድ ህፃን ልጅ ወደ ትምህርት ቤት  ከሄደ በኋላ የመጀመርያው አዕምሮውን የሚያዳብርበት ዘዴ መሆን ያለበት ብዙ  ቃላትን  መስማት ነው ። ንግግርን : በማበረታታት ፣ የነገሮችን አገላለፅ  በግልፅ በሚሠማ ቅላፄ  እና በእውነተኛ አጠቃቀማቸው በመናገር (ብዙ  አዋቂዎች ህፃናትን በህፃናት ድምፅ እና ኩልትፍና ማናገር የተለመደ እንደሆነ አይዘንጋ ( baby talk) በመዝሙር ፣ በተረት ፣ በቀላል መስተጋብራዊ አረፍተ ነገሮች ፣ በግጥሞች ፣ የልጆች የመጀመርያ የትምህርት ወቅቶች መቃኘት አለባቸው ። ይህ  የ ቃላት ካዝናቸውን ያዳብራል።

ከነዚህ : ከሠሙት ቃላት ታድያ : አንድ ፊደል መዘን  ስናሣያቸው  ያንኑ  የሚያውቁትን የሰሙትን የሚጠቀሙበትን ድምፅ ቅርፅ (symbol) እናሣያቸዋለን፤ ስለዚህ በቀላሉ  ይይዙታል ። ይህን ያወቁትን ፊደል ደግሞ ለብቻው  ተለይቶ  በመደብ ላይ በመቀረፅ ( ብዙ ግዜ በአሸዋ ወይም በብርጭቆ ወረቀት ይሠራል ) ይዳስሱታል ። በመጠቆሚያ እና በመሀል ጣታቸው ጫፍ እየዳሰሱ : ፊደሉን መንካታቸው : እጃቸውን : ያ ፊደል በሚፃፍበት  ቅርፅ  እና አቅጣጫ የእጆቻቸው ጡንቻዎች እንዲቀኙ ያለማምዳቸዋል ። ከትንሽ ልምምድ በኋላ  ህፃናቱ በራሳቸው የዕድገት መሠላል መሠረት ለመፃፍ  በጣም ስለሚጓጉ በቀላሉ የሚያሠፍሩበት ሠሌዳ  እና ቾክ በመስጠት እንዲፅፉ እናበረታታቸዋለን ።  ዶ/ር ሞንቴሶሪ ይህንን የፅሁፍ ጉጉት  ዕድሜ ( explosion into writing ) ትለዋለች ። የበለጠ ቃላት እና ፅሁፍ ባደረጉ ቁጥር ከፊደል የዘለለ ቃላትን ወደመፃፍ ፍላጎት ውስጥ ይገባሉ ። ታድያ 1 ፊደል ለብቻው የታተመ( movable alphabets) ብናቀርብላቸው በራሳቸው የሚያስቡትን ማንኛውንም ነገር እንዲፅፉ መንገድ ከፈትን ማለት ነው ። እርግጥ ነው : ከላይ እንደተጠቀሠው : በአሸዋ ወይም በብርጭቆ  ወረቀት የታተመ  ፊደል ለመስራት ቀላል ቢሆንም የወላጆችን ግዜ እና አቅም (resource) የሚገድብ እንዳይሆን ደግሞ በቀላሉ  ፊደሎቹን ራሱ አትሞ  ለየብቻ በመቆራረጥ መጠቀም እንደሚቻል  ሣልገልፅ አላልፍም ::

ሌላው ከቋንቋችን : ውጪ : የሆነን : ሌላ ቋንቋ ምሳሌ እንግሊዘኛ ፅሁፍ ለማስተማር ዋናው እክል  ከላይ እንደተጠቀሰው በህፃኑ ( ኗ ) ዙሪያ የማይነገር በመሆኑ  ድምፃቹን ባለማወቃቸው የመጀመሪያው ተግዳሮት ከዚህ ይነሳል። በ ትምህርት ቤት ውስጥ ደግሞ ከድምፀት ማጣራት ሳይሆን ከ symbol ( ከፊደል ) ወይም ከሁለቱ ጥምረት ስለሚጀምር ትንሽ ያዳግታቸዋል ። ስለዚህ : ሌላ ቋንቋ : ለማስተማርም ቢሆን ያላቸው : የቃላት : ሀብት መሠረታዊ : ስለሆነ : መጀመርያ : ከቃላት ሀብት ብንጀምር : መፃፍ የግድ በፍላጎት : ይከተላል ማለት ነው ።

ስለዚህ : እንደ ወላጅ ወይም አስተማሪ : በመጀመርያ መከተል : ያለብን መፍትሄ : ልጆች በቂ ቃላት : እንዲኖራቸው : ማናገር ፣ እንዲናገሩ ማበረታታት ፣ ታሪኮችን ማንበብ በመዝሙር/ በግጥም አብረን ግዜ ማሣለፍ ቅድመ እርምጃ ነው። ወደ መፃፉ : ስንገባ ደግሞ ከነዚሁ  ከሚያውቁት  ደጋግመው ከሚጠቀሙት ድምፆቹን ካጣሩት ቃላት ብንጀምርላቸው ፍላጎታቸውን ማነቃቃት እንዲሁም የቃላትን ምስረታ ስኬት ልናሳያቸው እንችላለን ። ፅሁፍን እንደ : መጤ ነገር : ሣይሆን በቃላት እየተናገሩት ያሉትን ነገር በ symbol የሚገልፁበት መሣርያ : መሆኑን ከተረዱ : በፍቅር ይወጡታል ።

ይቆየን!


https://www.youtube.com/watch?v=XHOmBV4js_E

ሀሳብ: ከዚህ ጽሁፍ ጋር የተያያዘው ቅርጽ በ ሞንቴሶሪ መማርያ ክፍል ውስጥ የምንጠቀምበት ሲሆን በየቤታችን ግን ይህን ዘዴ ለልጆቻችን መጠቀም ለምንፈልግ ሁሉ የተለያዩ ቅርፃችን ልክ ፊደላት በሚፃፉበት አቅጣጫ ከታች ወደላይ ዚግዛግ በመስራት ቅድመ ጽሁፍ የእጅ ማፍታቻ ልንሰራ እንችላለን ። ይህ በተለይም የእንግሊዘኛ ከርሲቭ አጻጻፍን ለመጀመር ጥሩ ድጋፍ ነው። ከዚህም ሌላ እንደ ልብስ ማጠብ፣ መወልወል፣ መጥረግ የመሳሰሉት የለት ተለት የህይወት ድርጊቶች የእጅ መገጣጠሚያን ስለሚያፍታቱ ምርጥ ቅድመ ጽሁፍ አነቃቂዎች ናቸው። ስለዚህ እኛ ወላጆች ለልጆቻችን እነዚህን ድርጊቶች ደጋግመው እንዲፈጽሙ መፍቀድ የውዴታ ግዴታችን ነው።