የዕለት ተዕለት ህይወት ክፍል ቅኝት

 በ ሞንቴሶሪ ክፍል ፡ ውስጥ

 (Practical life activities)

ከ 3-6 ዕድሜ ክልል ፡ ውስጥ ያሉ ህፃናት ወደ ፡ “ልጆች ቤት” (casa de bambini) ሲመጡ ፡ በመጀመርያ ፡ የሚለማመዱበት / የሚያዘወትሩት ፡ ክፍል ፡ የ ዕለት ፡ ተለት ተግባር ክፍል ፡ እንለዋለን፡፡ በዛሬው ፅሁፉችን ፡ ይህ ክፍል ፡ ምን እንደያዘ ፡ ምን ፋይዳ ለልጆች እንዳለው ፡ በ አጭሩ እናያለን።

ይህ የ ዕለት ተለት ህይወት ክፍል ፡ (practical life area) ህፃናት ፡ በዙሪያቸው ፡ ያሉት ፡ አዋቂ ፡ ሰዎች የሚከውኑትን ፡ እያንዳንዷን ፡ እንቅስቃሴ ፡ እነሡም ፡ በ አቅማቸው ፡ በማድረግ ፡ እራሳቸውን ፡ ለነፃነት የሚያዘጋጁበት ፡ ጅማሮ ነው። ለዚህ ፡ ክፍል ፡ በተመደበው ቦታ ላይ ፡ የመወልወል ፣ የመጥረግ ፣ የራስ ፡ እንክብካቤ ፣ የአካባቢ ፡ እንክብካቤ ፣ ቀዳሚ መሠረታዊ ፡ እንቅስቃሴዎች ፡ እንደ መክፈት/መዝጋት ፣ መቅዳት የመሳሰሉት ይጠቃለላሉ።
 
እነዚህ ድርጊቶች ፡ ለልጆች ፡ በሚመጥን ሁኔታ ፡ በሚደርሱበት በሚወዱት አቀራረብ በአሻንጉሊት ሣይሆን ፡ በእውነተኛ ዕቃዎች ፡ ተዘጋጅተው ፡ ለልጆች ተደራሽ ሲደረጉ ፡ የ ልጆችን ፍላጎት በመቀስቀስ ፡ እራሣቸው ፡ ዕቃዎቹ ፡ አስተማሪ ፡ ሆነው ፡ ይቀርባሉ።

ልጆቹም ይህ ፡ ላሉበት ፡ የዕድገት ደረጃ ፡ በጣም አስፈላጊ ፡ የነፃነት ፡ መውጫ ፡ መንገድ በመሆኑ ፡ ምክንያት ፡ በልዩ ፡ ተመስጦ ፡ እየከወኑት ፡ ለረጅም ሠዓት ፡ በመደጋገም ውስጥ ሆነው ፡ ሲለማመዱት ፡ እየተካኑበት ይሄዳሉ። ይህም በ አዋቂዎች ላይ ያላቸውን ጥገኝነት ፡ በማንሣት ፡ በራሣቸው አቅም ፈፃሚ/አድራጊ/ወሣኝ እንዲሆኑ እና ኀላፊነትን ለመውሠድ የማያቅማሙ ያደርጋቸዋል።

ለምሣሌ ፡- የ button frame ( የቁልፍ ፍሬምን ) ልምምድን ብንወስድ ፡ ልክ ለልብስ የምንጠቀማቸው ቁልፎች ፡ በፍሬም ላይ ተወጥሮ ፡ በተዘጋጀ እቃ ተቀምጠዋል። ህፃናቱ ፡ ይህን ቁልፍ ፡ መክፈትና መዝጋት ፡ በሠለጠነ አስተማሪ ፡ አጠቃቀሙ ፡ በድርጊት ፡ ከተገለፁላቸው በኋላ ፡ እነሡ በራሣቸው ፍላጎት እስከሚያቆሙ ድረስ ፡ በድግግሞሽ ይጠመዱና ፡ ይለማመዱታል። ይህም ፡  በ1 ቀን ተሞክሮ የሚያቆም ሳይሆን ፡ ቁልፍ መክፈትና መዝጋት ያለ ችግር  እስኪያደርጉት ድረስ የሚገፉበት ይሆናል ፤ ታድያ ተጠይቀውና ተገደው ሣይሆን ፡ በራሳቸው ከውስጥ በመነጨ ግፊት ያደርጉታል።

ይህም ፡ የራሣቸውን ልብስ ፡ ያለ አዋቂ አጋዥነት ፡ እንዲለብሡ ፡ ያግዛል ፤፡ በራስ መተማመናቸው ደግሞ ለሌላው ፡ ሙከራ ላይ ላለ ህፃን ምሳሌ ፣ አነሳሽ  ( አበረታች )ይሆናል ።  ታድያ በአንድ ድንጋይ ፡ ከአንድ ፡ በላይ ወፍ አያስብልም? 

 በራስ ፡ መተማመንን ገንብተው ፣ በተደጋጋሚ ሙከራ ውስጥ ፡ ጥረትን ፡ ትኩረትን ፡ አዳብረው ፣ የጥረት ውጤት በስኬት ሲዘጋ ተገንዝበው ፣ ያፈሱትን በረከት ፡ ተመልከቱ ።

ታዲያ ፣ የዕለት ተለት ህይወት እንቅስቃሴዎች ውስጥ የምናገኘው ቁልፍ ፡ ፍሬምን ብቻ አይደለም ፤ እዚህ ጋር ለምሣሌ አንድ መዘዝን እንጂ።

የ ዕቃዎቹ ፈርጅ ፡ ብዛት ፣ ዓይነት ፣ ባህልን ( የአካባቢውን ዘዬ የያዙ መሆናቸው ) ፣ ማራኪ ( ውብ ) መሆናቸው ፣ በልጆች ፡ ቁመትና ይዘት መመጠናቸው ፣ የህፃናትን የነፃነትን ጉዞ ፡ በተለያየ ፡ ሁኔታ ያማከሉ ፡ መሆናቸው ህፃናት ፡ በጉጉት እንዲጠቀሟቸው ብሎም ለራሣቸው ፣  እና ለአካባቢያቸው ፡ አስተዋፅኦ ማድረግ የሚችሉ ፡ የ ህብረተሰቡ ክፍሎች እንደሆኑ እንዲሰማቸው ያደርጋቸዋል። እያንዳንዱ በዚህ ክፍል የሚቀመጥ ዕቃ ከ ዕለት ኑሮአቸው ጋር ተያያዥነት ያለው በመሆኑ የተቀናጀ እንቅስቃሴ ( ሃሳብና ድርጊት ) ፣ ነፃነት የማግኘት ( እራስን እና አካባቢን መርዳት ) ፣ የጎለበተ ቋንቋ ባለቤት ለመሆን እና ሂወታቸውን ሙሉ አብሯቸው የሚዘልቀውን የቀንተቀን ኀላፊነትን መወጣት እንዲያዳብሩ ወሳኝ መሰረት ይጥላል።

እጅግ የሚያስገርመው ደግሞ ከዚህም ሌላ የዕለት ተለት ህይወት እንቅስቃሴዎች ልጆች የሚጠቀሙት የ motor skill (የ ሞቶር መዳበር) አንቀሳቃሽ በመሆኑ ለመፃፍ የምንጠቀምበትን የሰውነት ክፍል ስለሚያነቃቃ ልጆች ወደ መፃፍ ሲሻገሩ ክህሎቱን በቀላሉ ይወጡታል

ይህ የዕለት ተለት ህይወት ክፍል እንቅስቃሴ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ፡ የትብብርን መንፈስ አስፍቶ ፣ የባለቤትነት ስሜት ፡ ተክሎ ፡ ራሣቸውን ፡ ከተፈጥሮና ከአካባቢያቸው ጋር አቆራኝቶ ፡ ነፃና ሃላፊነት የሚወስድ ሰው በመሆን የስብዕናቸውን ፡ መሠረት ፡ በዚ በትንሽ እድሜያቸው ወደ ውስጣቸው እንዲያስገቡ ያግዛል።

ታዲያ ከዚህ በላይ ፡ ምን ፡ የመልካም ጅማሮ ፡ መሠረት ይኖራል?

ማጠቃለያ ሀሳብ ፡-

ይህ የዕለት ተለት ህይወት ክፍል ፡ ግዴታ ፡ በሞንቴሶሪ ትምህርት ቤት ውስጥ ፡ ብቻ የሚወሰን ሣይሆን ፡ ልጆቻችንን የራሳችን ፡ የዕለት ተለት ፡ ኑሮ ተካፋይ እንዲሆኑ በማድረግ ፣ ተዉ አትንኩ የሚለውን አግዙ በሚል ቃል እና ዲጂታል በመለወጥ እንደ  አቅማቸው በራሳቸው እንዲለብሱ ፣ እንዲጎርሱ ፣ እንዲያፀዱ ፡ መፍቀድ ፡ በቀስታ ፡ በማሳየት ፡ ድርጊቱን እንዲወጡ ማብቃት የወላጅ ( አሣዳጊ ) ኀላፊነታችንን እንወጣ እላለሁ።

ይቆየን!